አቢሲኒያ የኢንዱስትሪ ሽልማት ድርጅት “ትጉኃንን እንሸልማለን” በሚል መሪ ቃል ለ2016 ዓ.ም ባዘጋጀው የሽልማት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የዳይመንድ ደረጃ የወርቅ ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
የሽልማት ድርጅቱ መልካም የስራ አፈፃፀም ያላቸውን የመንግስት እና የግል ተቋማት ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ በኢንተርላግዠሪ ሆቴል ባዘጋጀው ስነስርኣት ሸልሟል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ የዳይመንድ ደረጃ የወርቅ ዋንጫ ሽልማቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር መስፍን ነገዎ ከዕለቱ የክብር እንግዳ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እጅ ተቀብለዋል፡፡
በተጨማሪም የተቋሙ ሶስት ከፍተኛ አመራሮች እና ሰባት ሰራተኞች የ”ትጉኃንን እንሸልማለን” መርሃግብሩ የወርቅ ኒሻን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
ተቋሙ ለሽልማት የበቃው ባለፉት አምስት አመታት በምዝገባና ስታንዳርዳይዜሽን እንዲሁም በግንባታ ቁጥጥር ዘርፎች ባስመዘገበው መልካም የስራ አፈፃፀም ነው፡፡
በዋናነትም የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ቀልጣፋ በማድረግ ረገድ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ 26 የአገልግሎት አይነቶችን ለተገልጋዮች ባሉበት ሆነው በኦንላይን አገልግሎትን ተደራሽ ማድረጉ ተጠቃሽ ነው፡፡
በዚህም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቅርቡ ባካሄደው ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ 2024 በዲጂታል ዘርፍ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው አገልግሎቶችን መጠቀም በማስቻል ረገድ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በምዝገባና ሰርተፍኬሽን አገልግሎት ተቋሙ ከ150 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎች ስራ ተቋራጮች እና አማካሪዎች አገልግሎት ሰጥቷል፡፡
ተቋሙ ባለፉት አምስት አመታት 801 የመንግስት ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የቁጥጥር ስራ አከናውኗል፡፡ በተለይም በዋጋ ግሽበት፣ በውል ብልሽት እና ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች ለበርካታ አመታት በጅምር ቀርተው የነበሩና የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው 758 የከፍተኛ ት/ት ተቋማት የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ተቋሙ ያካሄደው ጥናት ለመንግስት ውሳኔ በቀረበው መሰረት ማስተካከያዎች ተከናውነው ዳግም ወደ ግንባታ ከገቡት ውስጥ ከ500 በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለሀገርና ለህዝብ ግልጋሎት እንዲበቁ ተደርጓል፡፡
ሁላችንም እንኳን ደስ ያለን።